Tuesday, March 10, 2020

ምኩራብ


የዓብይ ጾም ሦስተኛ ሳምንት
  •   ምኩራብ ማለት የአይሁድ መቅደስ፣ ቤተ ጸሎት እንዲሁም ታላቅ አዳራሽ ማለት ሲሆን ለአምልኮና ለትህምህርት መማሪያ ይገለገሉበት ነበር፡፡ ምኩራብ በአለቆች ይመራ ነበር፡፡ (ማር 5÷22፣ ዮሐ 3÷14-15,18÷8) በእየሳምንቱ ሕዝቡ ሁሉ በምኩራብ ይሰበሰቡ ነበር (ሉቃስ 4÷16፣ የሐ.ሥ 15÷21) ወንዶችና ሴቶች ለእየብቻቸው ይፀልዩና ይቆሙ እንዲሁም ይቀመጡ ነበር፡፡
  • ታዲያ ይህ ሳምንት ለምን ምኩራብ ተባለ? ሲባል ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምዋለ ስብከቱ ለማስተማር ወደ ምኩራብ ገብቶ ነበርና ለዚያ መታሰቢያ እንዲሆን ምኩራብ ተብሏል (ማቴ 4÷23፣ ማር 1÷21፣ ሉቃ 4÷15)

ቅድስት


የዓቢይ ጾም ሁለተኛ ሣምንት ቅድስት ይባላል፡፡

  • ቅድስት ማለት የተቀደሰች፣ የተባረከች፣ ንጽሕት፣ ልዩ የተመሰገነች ማለት ነው፡፡
  • ቅድስት የተባለበት ምክንያት ‹‹ጾምን ቀድሱ ጉባኤውንም አውጁ ሽማግሌዎችንና በምድር የሚኖሩትን ሁሉ ወደ አምላካችሁ ወደ እግዚአብሔር ቤት ሰብስቡ (ኢዩ 1÷14) ብሎ በነቢዩ በኢዩኤል አድሮ የተናገረ ቅዱስ እግዚአብሔር ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጾማት ጾም ስለሆነች ቅድስት ትባላለች፡፡
  • እንዲሁም የዲያብሎስን ፈተና ድል ለመንሳት በቅድስት ከተማ በኢየሩሳሌም በሰሎሞን ቤተ መቅደስ ጫፍ የቆመባት ዕለት ሰው ጾምን ጾሞ እንደፈጣሪው ፈተናን ድል ነስቶ ቅድስናንና ክብርን ያገኛል፡፡ ለምን ብየ ቅድስቴን ጾምኳት እንዲሉ መጾም ቅድስናን ለማግኘት ነውና፡፡

Wednesday, February 26, 2020

ጾመ ኢየሱስ

ክብር ይግባውና ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጾው ጾም ‹‹ጾመ ኢየሱስ›› ይባላል፡፡
  • ጾም ‹‹ጾመ ጦመ›› ከሚል የግእዝ ግሥ የወጣ ሲሆን፣ ጾመ ማለት እህል ውሃ ሳይቀምስ   ዋለ፣ ሥጋ ከቅቤ ተከለከለ ማለት ነው፡፡(ትን. ዳን 10÷3)
  • ጸም ጦም ማለት ሲሆን ጊዜ ሳይደርስ እንዳይበላ፣ እዳይጠጣ የሚከለክል ሕግ በቅዱስ መጽሐፍ የታዘዘ የጸሎት ወንድም ማለት ነው፡፡ (ተን. ኢዩ 1÷14፣ 2÷15)
  • ጾም ቤሌላ አነጋገር ልጓም ይባላል፡፡ ይህም ቅዱስ ያሬድ በጾመ ድጓ መጽሐፉ ‹‹ጾም ልጓም ፍሬሐ ጥዑም ትሕተ ኢናምስላ ለጾም ትርጉም ጾም ልጓም ናት ፍሬዋም ጣፋጭ ነው ጾምን የተናቀች አናድርጋት (ጾመ ድጓ) ከሚለው የተወሰደ ነው፡፡ ልጓም የሰም አነጋገር ሲሆን ጾም ወርቅ ነው፡፡ ጾም ልጓም ናት ማለቱ በልጓም ፈረሶች ይገታሉ በጾምም የሰው ልጅ ሰውነቱን ከኀጢያት ሥራ ይገታበታልና፡፡ ፍሬዋም ጣፋጭ ነው ማለቱ ጹመን የምናገኘውን ክብር መግለጡ ነው፡፡ ስለ ጾም ባጭሩ ይህንን ካልን ስለ ጾመ ኢየሱስ እንቀጥላለን፡፡
             ጾመ ኢየሱስ የተለያዩ ስሞች አሉት
1. ጾመ ኢየሱስ ይባላል

         ጾመ ኢየሱስ የተባለበት ምክንያት ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተጠመቀ በኃላ ወደ ገዳመ ቆሮንቶስ ሄዶ በዚያ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ከዘረጋ ሳያጥፍ ከቆመ ሳይቀመጥ እሱ ራሱ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ከርስቶስ የጾመው ጾም ስለሆነ ነው፡፡