Tuesday, March 10, 2020

ቅድስት


የዓቢይ ጾም ሁለተኛ ሣምንት ቅድስት ይባላል፡፡

  • ቅድስት ማለት የተቀደሰች፣ የተባረከች፣ ንጽሕት፣ ልዩ የተመሰገነች ማለት ነው፡፡
  • ቅድስት የተባለበት ምክንያት ‹‹ጾምን ቀድሱ ጉባኤውንም አውጁ ሽማግሌዎችንና በምድር የሚኖሩትን ሁሉ ወደ አምላካችሁ ወደ እግዚአብሔር ቤት ሰብስቡ (ኢዩ 1÷14) ብሎ በነቢዩ በኢዩኤል አድሮ የተናገረ ቅዱስ እግዚአብሔር ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጾማት ጾም ስለሆነች ቅድስት ትባላለች፡፡
  • እንዲሁም የዲያብሎስን ፈተና ድል ለመንሳት በቅድስት ከተማ በኢየሩሳሌም በሰሎሞን ቤተ መቅደስ ጫፍ የቆመባት ዕለት ሰው ጾምን ጾሞ እንደፈጣሪው ፈተናን ድል ነስቶ ቅድስናንና ክብርን ያገኛል፡፡ ለምን ብየ ቅድስቴን ጾምኳት እንዲሉ መጾም ቅድስናን ለማግኘት ነውና፡፡
  •   ታዲያ ይህቺ የጌታችን ጾም ቅድስት ተብላ መጠራቷ የሚጾማትን ስለምትቀድስ ነው፡፡
  •  የቅድስት ትርጉም የተባረከች፣ ንጽሕት፣ ልዩ፣ የተመሰገነች ነው ብለናልና ስለዚህ የሚጾማትን ትባርካለች፣ ንጹሕ ታደርጋለች፣ ከኃጢአት የተለየ ታደርጋለች በመጨረሻው ዘመን ጌታችን ሲመጣም በቀኝ ቁም ‹‹እናንተ የአባቴ ብሩካን›› የሚለው የምስጋና ድምጽ እንዲሰማ ታደርጋዋለች፡፡ ቅዱስ ያሬድም በጾመ ድጓው ‹‹ጾም ቅድስት በቁዔት ባቲ ትፈሪ ለነ አስካለ በረከት ወት ዔሥዮሙ ጽድቀ ለቅዱሳን ትርጉም ‹‹ጾም ቅድስት ናት ጥቅም አለባት የበረከት ፍሬን ታፈራልናለች ለቅዱሳንም ጽድቅን ትሰጣቸዋለች›› እንዳለ (ጾመ ድጓ) የምንጾመው ዝም ብሎ ሥጋን ለማስራብ፣ ለማድከም ሳይሆን መግሥተ ሰማያትን ለመውረስ  እና በረከተ ሥጋንም በረከተ ነፍስንም ለማግኘት ነው፡፡
2. ሰንበት ቅድስት ትባላለች፡፡
‹‹ ለእግዚአብሔር ሰባተኛይቱን ቀን ባረካት ቀደሳት›› (ዘፍ 2÷3፣ ዘፀ 20÷8) ሰዎች ፍጥረት ያለተፈጠረባት ዕለት ናት ብለው እንዳይንቋት እንዳያቃልሏት እረፍተ ሥጋ እረፍተ ነፍስ የተገኘባት ዕለት ስለሆነች ቀደሳት አለ፡፡ ቅዱስ ያሬድም ‹‹ሰንበትየ ቅድስትየ እንተ አዕረፍኩ እምኩሉ ግርዬ ይቤ እግዚአብሔር›› ትርጉም ከሥራየ ሁሉ ያረፍኩባት ሰንበት ቅድስት ናት አለ እግዚአብሔር›› (ጾመ ድጓ) ብሎ ጀምሯል፡፡ እኛም ክርስቲያኖች እግዚአብሔር እንድትከብር የተናገራላት ሰንበትን አክብረን የደቅድስና ባለቤት የሆነ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ፈጽመን ቅድስናን ለማግኘት መሸቀዳደም አለብን፡፡ በዓላትን ስናከብር እግዚአብሔርን ማክበራችን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ መፈጸም ነውና ‹‹እመሰ ታፈቅሩኒ ኒእቀቡ ትእዛዝየ ብትወዱኝስ ትእዛዜን ጠብቁ›› (ዮሐ 14÷15) አንዲል፡፡

         በመጋቢ ሀዲስ መምህር ዳንኤል አለባቸው

No comments:

Post a Comment