Tuesday, March 10, 2020

ምኩራብ


የዓብይ ጾም ሦስተኛ ሳምንት
  •   ምኩራብ ማለት የአይሁድ መቅደስ፣ ቤተ ጸሎት እንዲሁም ታላቅ አዳራሽ ማለት ሲሆን ለአምልኮና ለትህምህርት መማሪያ ይገለገሉበት ነበር፡፡ ምኩራብ በአለቆች ይመራ ነበር፡፡ (ማር 5÷22፣ ዮሐ 3÷14-15,18÷8) በእየሳምንቱ ሕዝቡ ሁሉ በምኩራብ ይሰበሰቡ ነበር (ሉቃስ 4÷16፣ የሐ.ሥ 15÷21) ወንዶችና ሴቶች ለእየብቻቸው ይፀልዩና ይቆሙ እንዲሁም ይቀመጡ ነበር፡፡
  • ታዲያ ይህ ሳምንት ለምን ምኩራብ ተባለ? ሲባል ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምዋለ ስብከቱ ለማስተማር ወደ ምኩራብ ገብቶ ነበርና ለዚያ መታሰቢያ እንዲሆን ምኩራብ ተብሏል (ማቴ 4÷23፣ ማር 1÷21፣ ሉቃ 4÷15)

  • ወደ ዚህም ምኩራብ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አንድ ቀን ሊያስተምር ሲገባ አይሁድ ቤተ ጸሎቱን እንደ ስያሜው ሳይሆን መሸጫና መለዋወጫ፣ መገበያያ አድርገውት ስለአገኛቸው ‹‹ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል እናንተ ግን የወንበዴዎች ዋሻ መሸጫ መለዋወጫ አድረጋችሁት›› ብሎ ሰዎችንና እንስሶችን ጅራፍ አበጅቶ አስወጣቸው ገበታቸውን እየገለበጠ አባሯቸዋል፡፡ ስለዚህ ይህ ሳምንት ለታሪኩ መታሰቢያ ምኩራብ ተብሏል (ማቴ 21÷12-13፣ ማር 11÷15-48፣ ሉ 19÷45-47፣ የሐ 2÷14-16) በኃላም ሐዋርያት እንደ ጌታችን ለጸሎትና ለትምህርተ ወንጌል ወደ ምኩራብ ይሄዱ ነበር (የሐዋ.ሥ 3÷1፣13 ÷5፣ 14÷1፣ 17÷1፣ 10÷17፣ 18÷4፣19÷8)                                    ከዚህ ታሪክ ምን እንማራለን፡-
1.  ቤተ ክርስቲያን የጸሎት፣ የአምልኮት፣ የምስጋና ቦታ፣ የትምህርተ ወንጌል መማሪያ፣ አስቀድሰን ሥጋውን ደሙን የምንቀበልበትና ንሰሐ ገብተን ከእግዚአብሔር ጋር የምንገናኝበት ጠቅለል ባለ አነጋገር መንፈሳዊ ሥራ እንጂ ሥጋዊ ሥራ የማይሰራበት አግዚአብሔር ከቅዱሳን መላእክትና ከቅዱሳን ሰዎች ሁሉ ጋር የሚገኝበትና በመንፈሳዊ ሕይወት በውጊያ ላይ ያለችው ቤተ ክርስቲያን ውጊያውን ከአሸነፈችው ቤተ ክርስቲያን ጋር ሕብረት የምታደርግበት መሆኑን እንማራለን
2.  በቤተ ክርስቲያን ዙሪያ የሥጋ ሥራ ማለትም ሥጋዊ ስብሰባ ማድረግ አሁን በእየቤተ ክርስቲያኑ ዙርያ እንደሚደረገው ገበያ ማድረግ የተከለከለና እግዚአብሔርን የሚያሳዝን መሆኑን እንዲሁም ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን ይጠብቁ ዘንድ እንደሚያስፈልግ እንማራለን
3.  ቤተ መቅደስ የተባለ የእኛ አካል ነውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእኛን ሥጋ ለብሶ በምድር እየተመላለሰ በሚያስተምር ጊዜ ሰው ሁሉ የኃጢያት መገበያያ መሸቀጫ ሆኑ ማግኘቱን ለቤተ መቅደሱ ቀንቶ ሻጮችን ለዋጮችን እንዳስወጣ ሁሉ ቤተ መቅደስ ስለተባለ አካላቻንም ቀንቶ ከኃጢአት እንድንወጣ ወንጌልን ማስተማሩን ስለእኛ ራሱን አሳልፎ ለሞት መስጠቱን እኛን ከኃጢአት ማንፃቱን እናምናለን፡፡
እናም ጌታችን መድኃኒታችን ኢሱስ ክርስቶስ የሚቀናለት ቤተ መቅደስ ሰውነታችንን ከኃጢያት ልጠብቀውና ኃጢአትም ብሠራ እንኳ በንሰሐ ልናነጻው ያስፈልጋል፡፡

      በመጋቢ ሀዲስ መምህር ዳንኤል አለባቸው

No comments:

Post a Comment